
ስለ ታላቋ ኢትዮጵያ ማወቅ ያለብዎት አስገራሚ ጉዳዮች
ኢትዮጵያ በአፍሪካ ቀንድ የምትገኝ የረጅም ዘመን ታሪክ ያላት ሀገር ናት። በአፍሪካ ነፃነታቸውን ጠብቀው ለመኖር ከቻሉ ሁለት አገሮች አንዷ ነች። በህዝብ ብዛት ከአፍሪካ ኢትዮጵያ ሁለተኛ ስትሆን ፣ በቆዳ ስፋት ደግሞ አስረኛ ናት። ዋና ከተማዋ አዲስ አበባ ናት። አብዛኛዎቹ የአፍሪካ ሀገሮች ዕድሜያቸው ከአንድ ምዕተ-ዓመት የሚያንስ ሲሆን ፣ ኢትዮጵያ ግን ከጥንት ጊዜ ጀምሮ በንጉሠ-ነገሥታት እና ንግሥተ-ነግሥታት የተመራች ሀገር ናት። የሰለሞናዊው ሥርወ-መንግሥት የአመጣጡን ዘር እስከ አስረኛው ዓመተ-ዓለም ድረስ ይቆጥራል። ኢትዮጵያ የሰው ልጅ ከጥንት ጊዜ ጀምሮ የኖረባት ቦታ እንደሆነች ብዙ የሳይንሳዊ መረጃ ተግኝቷል። በበርሊን ጉባኤ በኩል የአውሮፓ ሀያላት ሀገሮች አፍሪካን ሲከፋፍሏት፣ ኢትዮጵያ ነፃነቷን ጠብቃለች። የሊግ ኦፍ ኔሽንስ (League of Nations) አባል ከነበሩት ሶስት የአፍሪካ ሀገሮች አንዷ ነበረች። ከአጭር የኢጣልያ ወረራ ጊዜ በኋላም ከየተባበሩት መንግሥታት መሥራቾች አንዷ ናት። ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ ብዙ የአፍሪካ ሀገራት ነፃነታቸውን ሲያገኙ፣ ሰንደቅ-አላማቸውን በኢትዮጵያ ቀለሞች ማለትም በአረንጓዴ ፣ ቢጫ እና ቀይ ላይ ነው የመሠረቱት። አዲስ አበባ ደግሞ ለየተለያዩ በአፍሪካ ላይ ላተኮሩ አለም አቀፍ ድርጅቶች መቀመጫ ሆነች። የዛሬዋ ኢትዮጵያ የትልቅ የግዛት ለውጥ ውጤት ናት። ከሰሜን ግዛቱዋ በጣም የተቀነሰ ሲሆን በደቡብ በኩል ደግሞ ተስፋፍቷል። በ ፲፱፻፷፯ (1967) ዓ.ም.፣ ግርማዊ ቀዳማዊ ዓፄ ኃይለ ሥላሴ ከሥልጣን ሲወርዱ፣ የእርስ በርስ ጦርነት በሀገሩ ተባባሰ። ከዚህ ጊዜ በኋላ ኢትዮጵያ በተለያዩ የመንግሥት አይነቶች ተዳድራለች። ዛሬ አዲስ አበባ የአፍሪካ ሕብረት (African Union) እና የተባበሩት መንግሥታት የኢኮኖሚክ ኮሚሽን ለአፍሪካ መቀመጫ ናት። የኢትዮጵያ የመከላከያ ሠራዊት ከአፍሪካ ኃያል ሠራዊቶች አንዱ ነው። ኢትዮጵያ በአፍሪቃ የእራሷ ጥንታዊ ፊደል ያላት ሀገርም ናት። Wonchi Lake of Ethiopia.jpg ኢትዮጵያ ተፈጥሮ ያደላት ሀገር ናት። ከአፍሪካ ትላልቅ ተራራዎች እንዲሁም ከዓለም ከባህር ጠለል በታች በጣም ጥልቅ ከሆኑ ቦታዎች አንዳንዶቹ ይገኙባታል። ሶፍ ዑመር ከአፍሪካ ዋሻዎች ትልቁ ሲሆን ፣ ዳሎል ከዓለም በጣም ሙቅ ቦታዎች አንዱ ነው። ወደ ሰማንኒያ የሚቆጠሩ ብሔሮችና ብሔረሰቦች ዛሬ በኢትዮጵያ ይገኛሉ። ከእነዚህም ኦሮሞና አምሀራ በብዛት ትልቆቹ ናቸው። ኢትዮጵያ በኣክሱም ሓውልት፣ ከአንድ ድንጋይ ተፈልፍለው በተሰሩ ቤተ-ክርስትያኖቹዋ እና በኦሎምፒክ የወርቅ ሜዳልያ አሸናፊ አትሌቶቹዋ ትታወቃለች። የቡና ፍሬ ለመጀመሪያ ጊዜ የተገኘው በኢትዮጵያ ሲሆን ሀገሪቱዋ በቡናና ማር አምራችነት በአፍሪካ ቅድሚያ ይዛለች። ኢትዮጵያ ከዓለም ሶስቱ ትላልቅ የአብርሃም ሀይማኖቶች ጋር ታሪካዊ ግንኙነት አላት። ክርስትናን በአራተኛው ምዕተ-ዓመት ተቀብላለች። ከሕዝቡ አንድ ሁለተኛው ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ክርስትና ነው። የመጀመሪያው የእስላም ሂጅራ ወደ ኢትዮጵያ ነው የተከናወነው። ነጋሽ በአፍሪካ የመጀመሪያው የእስላም መቀመጫ ናት። እስከ ፲፱፻፸ ዎቹ ድረስ ብዙ ቤተ-እስራኤሎች በኢትዮጵያ ይኖሩ ነበር። የራስ ተፈሪ እንቅስቃሴ ኢትዮጵያን በትልቅ ክብር ነው የሚያያት።
ውክፔድያ